Welcome Home!

Welcome

ከሁሉ በማስቀደም የጌታችንና የመድኃኒታችን ጸጋና ሰላም ከእርስዎ ጋር ይሁን እያልሁ ከእኛ ጋር ይህን ድንቅ ጌታ አብረውን ስላመለኩ የተሰማኝን ትልቅ ደስታ ልገልጽልዎ እወዳለሁ፡፡ መድኃኔዓለም ወንጌላዊት ቤተክርስትያን ከ35 አመት በላይ በእግዚአብሔር ጸጋ በሲያትልና በአካባቢዋ ለቅዱሳንና ለአካባቢው  ህብረተሰብ የክርስቶስ ኢየሱስን ፍቅር ስታካፍል ቆይታለች፡፡

እንደማንኛውም የክርስቶስ ኢየሱስ ቤተክርስትያን መድኃኔዓለም ወንጌላዊት ቤተክርስትያን ጤናማ በሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮና እውነተኛ በሆነ የመንፈስ ቅዱስ እንቅስቃሴ ታምናለች፡፡  ኢየሱስ ክርስቶስ ለአካሉ ማለትም ለቤተክርስትያን የሰጣት መንፈሳዊ ስጦታዎች ሁሉ ዛሬም እንዳልተቃረጡና እንደሚሰሩ ከማመንም በላይ በአግባቡ መለማመድን ታበረታታለች፡፡ ቤተክርስትያኒቱ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጣትን ኃላፊነት ለመወጣት ቅዱሳን በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የሚያድጉበትን እንዲሁም እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ ውጤታማ ሆነው እንዲያገለግሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን፣ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲሁም በኮሌጅ ደረጃ የሚሰጡ ትምህርቶችን ጭምር ከመስጠትዋም በላይ ቅዱሳን ባሉበት ሁኔታ የሚረዱአቸውን የተለያዩ ትምህርቶችን የማማከር አገልግለቶችን ትሰጣለች፡፡ ቤተክርስትያናችን የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በመከተል ክርስቶስ የሰውን ሁለንተና ያገለግል እንደነበር ቤተክርስቲያኒቱም ለሁለንተናዊ አገልግሎት ትኩረት ትሰጣለች፡፡ ሰው መንፈስ ብቻ ሳይሆን ሥጋና ነፍስ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊና ማህበራዊ ፍላጎቶች ያሉት በመሆኑ የሰውን ሁለንተና ወይም ሙሉውን ሰው ማገልገል የሚለው መርህ  የአገልግሎታችን መልህቅ ነው፡፡

የታላቁን ተልዕኮ አደራ ለመወጣት ሰውን በሁለንተናው ማገልገል የሚለውን መርህ በማማከል በወንጌል ሥርጭት በአንድ በአንድም ሆነ በጀማ ስብከት ሰዎችን ለክርስቶስ ለመድረስ እንተጋለን፡፡ ይህ አገልግሎት ወይም የአንድና የሁለት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሥራ ሳይሆን እንደ ቤተክርስትያንና እንደ አንድ በክርስቶስ የዳነ አማኝ የሁላችንም የሥራ ድርሻ ነው፡፡ ከወንጌል ሥርጭቱ ጎን ለጎን እንደየግለሰቡ ሁኔታ ለወንጌል ሥርጭት ጥርጊያ መንገድ የሚያመቻች ወይም ፍጹም የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ለማሳየት የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንሰጣለን፡፡ ይህ ከጌታ የተሰጠን አገልግሎት ተያይዞ መሥራት የሚያስፈልገው በመሆኑ ቤተክርስትያኒቱ በጤናማ መንገድ ከተመሰረቱና ጤናማ አስተምህሮና ልምምዶች ካሉአችው በአሜሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ካሉ  ሌሎች አብያተክርስትያናትና ህብረቶች በሚያስፈልገው ሁሉ አብራ ትሰራለች፡፡
መድኃኔአለም ወንጌላዊት ቤተክርስትያንን ከሌሎች ለየት የሚያደርጋት ወደ ቤተክርስትያኒቱ የሚጨመሩ ሁሉ አባል ከመሆን በላይ ቤተሰብ እንዲሆኑ ማለትም በክርስቶስ ያለን ወንድምነትነትንና እህትነትን አጥብቀው እንዲይዙ፣ የእግዚአብሔር ቤት አዲስና የቆየ የሚባል መከፋፈያ ወይም ማንኛውም ግድግዳ የፈረሰበት ሁሉም  የባለቤትነት መንፈስ እየተሰማው ባለውና በተሰጠው ጸጋ ሁሉ አብሮ ለማደግና ለማገልገል የሚተጋ፣ ሰዎችን ለክርስቶስ ደቀመዛሙርት ለማድረግ በሚደረገው የተለያየ ጥረት ተመልካች/ታዛቢ ሳይሆን ያገባኛል/ይመለከተኛል እያሉ በዕውቀት፣ በችሎታ፣ በክህሎትና በገንዘባቸው ሁሉ በመሰጠት ተሳታፊ እንዲሆኑ ነው፡፡


በጌታ አገልግሎት

ዶ/ር ግርማ ደሳለኝ ዋና ፓስተር

Connect with us

Complete the form below and we’ll forward your inquiry to the appropriate team member.